አነስተኛ የይገባኛል ጥያቄዎች ፍርድ ቤት

አንድ ሸማች በሻጩ ላይ የይገባኛል ጥያቄን ክስ በሀሻሎም ፍርድ ቤት በኩል ማቅረብ ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ክስ በጠበቃ የታገዘ መሆን አለበት ። ሌሎች ለተጠቃሚዎች የሚዳኙ ፍርድ ቤቶች የአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤትና የተለያዩ የሚያገላግሉ አካላትም ይኖራሉ ።

ከ 1/1/24 ጀምሮ አንድ ሸማች የይገባኛል ጥያቄው መጠን ከ 37,700 ሸቄል የማይበልጥ ከሆነ በይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል ። ይህን ክስ ከማቅረቡ በፊት የአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት ጽሕፈት ቤቱን ወይም የሸማቾች ድርጅቶችን ማማከር ይመከራል

 

ለአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄዎች ፍርድ ቤት የተሰጡት ስልጣኖች

የአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት ሸማቹ ባቀረበው ብቁ የሆነ ማስረጃ ያለው ከሆነ ፤ ለሻጩ ፤ የተቀበለውን ገንዘብ እንዲመልስ ፤ ምርቱን በሌላ ምርት እንዲተካ ወይም እንዲጠግንና ግብይቱን እንዲሰርዝ ብሎ የመፍረድ መብት አለው

ያለ ጠበቃ ውክልና የሚደረግ ፍርድ

በትንሽ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት ውስጥ ያሉ ወገኖች ጠበቆችን እንዲጠቀሙ አይፈቀድላቸውም ፤ ነገር ግን በተለያዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቱ ይህን እንዲያደርጉ ሊፈቅድላቸው ይችላል

ክሱ የሚቀርበው የት ነው ?

በተጠቃሚውና በሻጩ መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት ክሱ መቅረብ ያለበት ቦታ ቢመደብም ቅሉ፤ ሸማቹ ክሱን ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ቦታዎች በአንዱ ለአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል ።

  • በተከሳሹ የመኖሪያ ቦታ ወይም የንግድ ቦታ
  • ሸማቹ የሚከስበት ድርጊት ወይም ስህተት በተፈጸመበት ቦታ
  • የይገባኛል ጥያቄ ውስጥ - ዋናውን የይገባኛል ጥያቄ ከማቅርብበት ቦታ

በኢንተርኔት ላይ በማስታወቂያ ወይም በንግድ ምክንያት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ የይገባኛል ጥያቄው የሚቀርበው ችሎቱ የከሳሹ ወይም የተከሳሹ የመኖሪያ ቦታ ወይም የንግድ ቦታ ብቻ ነው ።

 

የግብር ክፍያ

ለአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት የይገባኛል ጥያቄ ያቀረበ ሸማች በሕግ መሰረት የግብር ክፍያ መክፈል አለበት ።

የይገባኛል ክስ ጥያቄ መግለጫ ፤ የክሱ መከላከያ መግለጫና የፍርድ ቤት ሂደቶች

ሸማቹ ባቀረበው የይገባኛል ጥያቄ መግለጫ ውስጥ የእርሱን መግለጫ ዝርዝር ሁኔታዎችና የተከሳሹን ፤ ስም ፤ የመታዎቂያ / የመለያ ቁጥር (የግል የመታወቂያ ቁጥር ወይም የድርጅቱ ቁጥር) ፤ አድራሻና የመገናኛ ዘዴዎች ዝርዝሮችን መግለጽ አለበት በንግድ ሥራ ላይ በተመሰረተው ክስ ውስጥ በብዙ ጉዳዮች ላይ የንግዱን ባለቤትና / ወይም ተወካዩን ፤ እንደ ተከሳሾች አድርጎ ጨምሮ ማቅረብ በጣም ጠቃሚ ነው። የይገባኛል ጥያቄውን በድርጅቱ ባለቤት ወይም በድርጅቱ ተወካይ ላይ ስለማቅረብ ጥርጣሬ ካለ ምክር ለማግኘት ወደ ሸማቾች ማሕበር በመደወል አስተባባሪዎችን ማነጋገር ይችላሉ ።

በደብዳቤው ላይ የይገባኛል ጥያቄ አቅራቢው ሸማች የተፈፀመውን ግብይት መግለጽ ፤ የተፈፀመበትን ቀንና ቦታ መግለጽ ፤ የገንዘብ ጥያቄ ከሆነ የገንዘብ ይገባኛል ጥያቄውን መጠን መግለጽና የተጠየቀውን የማግኘት መብት ያለው ለምን እንደሆነ ማስረዳት አለበት (ካሳ ፤ የምርት መተካት ፤ ግብይቱን መሰረዝ ፤ ወ.ዘ.ተ.) ። ተከሳሹ በፍርድ ሂደቱ ላይ ሊተማመንባቸው የሚፈልጋቸው ሁሉም ሰነዶች በእጁ ውስጥ ካሉ የይገባኛል ጥያቄ መግለጫው ጋር በማያያዝ ለፍርድ ቤቱ መቅረብ አለባቸው ።

የይገባኛል ጥያቄው ከቀረበ በኋላ ተከሳሹ የይገባኛል ጥያቄው ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ የመከላከያ መግለጫ እንዲያቀርብና በፍርድ ቤቱ ጽሕፈት ቤት በተቀጠረበት ቀን ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ይታዘዛል ።

ፍርድ ቤቱ የተከራካሪ ወገኖች ማስረጃ የሚቀርብበትን ቅደም ተከተል ይወስናል። ክርክሩን በንቃት በማብራራት የተፈጠረውን አለመግባባት ማጣራት ይጀምራል ።

ፍርድ ቤቱ ከችሎቱ በኋላ የይገባኛል ጥያቄውን ይወስናል ፤ አንዳንድ ጊዜ ለሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሐሳብ ያቀርባል ፤ ይህ ስምምነት የፍርድ ውሳኔ ውጤትነት ይኖረዋል ፤ ፍርድ ቤቱ ፍርዱን በአጭሩ ማስረዳት አለበት ፤ ፍርዱ በሚሰጥበት ጊዜ ሁለቱም ወገኖች በተጠቀሰው የፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት መሥራት አለባቸው ።

 

ይግባኝ የማቅረብ ፍቃድ

በአነስተኛ የይገባኛል ጥያቄ ፍርድ ቤት፣ ፍርድ ላይ ይግባኝ ለማለት የሚፈልግ ወገን በክልሉ ወረዳ ፍርድ ቤት በመሄድ ማመልከትና ይግባኝ ለማለት የፍቃድ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል ። ይህንም ማድረግ የሚችለው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተወሰነና የውሳኔው ደብዳቤ ከእጁ ከገባ በ15 ቀናት ውስጥ ነው ።

 

 

 

በዚህ የመምሪያ መጽሔት ውስጥ የቀረበው መረጃ አጠቃላይ መረጃ ብቻ ነው ፤ ግን ሕጋዊ ምክርን የሚተካ አይደለም እና ያለ ተገቢ ምክር ብቻዉን መታመን የለበትም.
ይህ መምሪያ ሰኔ ወር 2023 ዓ.ም. ያለውን መረጃ በሕጉ እና ደንቡ ላይ በመመርኮዝ ተሻሽሏል ።
አስገዳጅ የሚሆነው የሕጉ እና የደንቡ ጽሑፍ ነው።